ከበረሃ ጠርቶኝ (ግጥም በአክሊሉ ፍስሐ) ከእናታቸው ማህጸን ተወልደው ከወጡት ከወንዶች መሀከል

መንገዱን ለማጽዳት በሰዎች ልብ ውስጥ ፍቅርን ለመትከል

ባሪያ ሁኜ ሳለሁ የጫማውን ጠፍር መፍታት ሳይገባኝ

እሱ ግን አክብሮ እኔን አስቀድሞ በመንገዱ መራኝ

ሂድና አጸዳዳው አባጣ ጎርባጣ ጥረግ ስንኩልኩሉን

በንስሃ አጥበህ ለመልካሙ ንጉሥ አዘጋጀው ሁሉን

ብሎ በለመለመው መስክ ላከኝ ከዮርዳኖስ

የሕዝቡን ልቦና አጥምቄ እንድመልስ

ክብር ሳይገባኝ በረኸኛ ሳለሁ ጠፍር ማገለድም

ከበረሃ ጠርቶ ለክብሩ መረጠኝ ቸሩ መድኃኔዓለም

ከእኔ አስቀድሞ የነበረው ጌታ ከኋላ ቢመጣም

መንሹ በእጁ ነው ገለባ ለይቶ ጎተራ ይከታል ያጠራል ሁሉንም

ምንም ሳይገባኝ እኔ ለንስሃ በውሃ ባጠምቃችሁ

የእግዚአብሔር ልጅ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በእሳት ሊያጠምቃችሁ

ከእኔ በፊትህ ያለው በዕድሜ የቀደምኩት ይመጣል ጌታችሁ

እናንተ

የእፉኝት ልጆች በልባችሁ ማሳ ቂም እየያዛችሁ ከደጁ ምትቆሙ

ለመዳን ብላችሁ ህሊናችሁ ታስሮ ነገር የምትለቅሙ

ከሚመጣው ቁጣ መሸሻውን ታዛ ማምለጪያ መንገዱን

ከስላቁ ቃሪሚያ ወዲህ ማን ጠራችሁ ማንስ ጠቆማችሁ የጌታ ሁዳዱን

ልባችሁ በዓለም በገንዘብ ተሰልቦ በኃጢአት እያደረ

በጠላት ተገዝቶ ግፍ እየገበረ

አብርሃም አብርሃም አብርሃም ብትሉ ሚሰማችሁ የለም

የአብርሃምን ምግባር ሠርታችሁ አሳዩ ትጉና በዓለም

ሰዎች ሆይ ተነሱ የመመለስ ዘመን ቀኑ ደርሷልና በጾም ጸሎት ትጉ

ለንስሐ የሚሆን የመዳኛን ምግባር መልካም ፍሬ አድርጉ

በእግዚአብሔር ጸጋ በለምለሙ መንገድ በፍቅር እደጉ

ተነሱ ! ጹሙና ጸልዩ ከኃጢአተኞች መንጋ ተለዩና ውጡ

የአምላካችሁን ቃል ሕያው የሆነውን ወንጌሉን አድምጡ

ምሣሩ በዛፍ ሥር ስሎ ተቀምጧል

ፍሬ የሌለውን መሀኑን ይቆርጣል

ስለዚህ የአብርሃም ወገኖች በአባታችሁ ምግባር እናንተ አትመኩ

በጽድቅ ለአምላካችሁ ለህያው እግዚአብሔር በክብር ተንበርከኩ

Start a discussion with Akibeth

Start a discussion